ዛሬ ዕለተ ሐሙስ አውስትራሊያ ውስጥ በኮቪድ - 19 የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 55, 602 ለሕልፈተ ሕይወት የተዳረጉ 89 ደርሷል።
ኩዊንስላንድ ከወርኃ ኤፕሪል ወዲህ ዕለታዊ የኮቪድ - 19 ተጠቂዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን አመልክታለች።
ምዕራብ አውስትራሊያ፣ ደቡብ አውስትራሊያ፣ ታዝማኒያ እና ኖርዘርን ቴሪቶሪ ባለፉት አራት ውስጥ የኮቪድ - 19 ሕሙማን ቁጥር ማሻቀቡን ገልጠዋል።
ወቅታዊ አዲስ ተጠቂዎች፣ የሆስፒታል ሕሙማን እና ሟቾችን መረጃ እዚህ ይመልከቱ .
አውስትራሊያውያን ተመራማሪዎች ኮቪድ - 19ን ጨምሮ ለተወሰኑ ጊዜያት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነ ባክቴሪያና ቫይሶች እንዳይዛመቱ ተረጪ መከላከያ ሠርተዋል።
የሲድኒ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች ተረጪ መከላከያው አማራጭ ከሆነው ፀረ - ሕዋሳት የተሻለ መሆኑን ገልጠዋል። የአሳንሱር መጫኛዎችና የደረጃ የጎን መጨበጫዎች ላይም መርጨት ይቻላል። እንዲሁም ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ በትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎችና ምግብ ቤቶች መጠቀም ይቻላል።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ ጤና በሳምንታዊ መግለጫው ሰባት የባሕር ማዶ ተመላሽ መንገደኞች በአዲሱ የኮቪድ BA.2.75 ዝርያ የተያዙ መሆናቸውን አመልክቷል። አዲሱ የኮቪድ ዝርያ በሌሎች ከአሥር በበለጡ አገራት ውስጥም የተከሰተ ሲሆን የጎጂነቱ መጠን ምን ያህል እንደሁ ለጊዜው አልታወቀም።
የኒው ሳውዝ ዌይልስ ጤና ባለፈው ሳምንት 142 ሰዎች በኮቪድ - 19 ሳቢያ ሕይወታቸውን እንዳጡ ጠቁሞ፤ ከሟቾቹ ውስጥ 96ቱ (ወይም 68 ፐርሰንቱ ብቻ የኮቪድ - 19 ሶስተኛ ዙር ክትባት እንደተከተቡና ሌሎች 46 ሰዎች ለሶስተኛ ዙር ክትባት መመዘኛዎችን ያሟሉ እንደነበር አስታውቋል።
በቀጣዩ የብሔራዊ ካቢኔ ስብሰባ ወቅትም መሪዎች ያለ ጠቅላላ ሐኪም ትዕዛዝ የኮቪድ - 19 ፀረ - ቫይረስ ኪኒኖችን ሊወስዱ ይገባ እንደሁ ይመክራል።
ትናንት ረቡዕ ዕለት የአውስትራሊያ የክትባት ቴክኒካዊ አማካሪ ቡድን የፈዋሽ ቁሶች አስተዳደር ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት የሞደርና ስፓይክቫክስ ክትባት እንዲሰጥ ጊዜያዊ ይሁንታን መቸሩን አስመልክቶ ለመምከር ታድሞ ነበር።
አማካሪ ቡድኑ ዳታዎቹን የገመገመ መሆኑን ጠቅሶ ምክረ ሃሳቡንም በመጪዎቹ ቀናት ለጤና ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ ገልጧል።
የኖርዘን ቴሪቶሪ ተጠባባቂ ዋና የጤና መኮንን ዶ/ር ቻርልስ ፓይን በረጅሙ ሳምንት መጨረሻ የሚካሔደውን የዳርዊን ትዕይንትን አስመልክተው አዲስ የኮቪድ ቫይረስ መከስትን ልብ ብለው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አበረታተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባወጣው (ጁላይ 11 - 17 / ሐምሌ 4 - 10) ሳምንታዊ ሪፖርቱ አዲስ የወረርሽኝ መስፋፋት ባለፉት አምስት ሳምንታት ካሻቀበ በኋላ ከፍ ሳይል መቆየቱን አመልክቷል።
ከፍተኛ አዲስ ሳምንታዊ የቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር እየተመለከተ ያለው ከዩናይትድ ስቴትስ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ጀርመንና ጃፓን ነው።