ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኒዚ አውስትራሊያ እስከ 2040 የሚዘልቅ ለደቡብ ምሥራቅ እስያ የነደፈችውን አዲስ ምጣኔ ሃብታዊ ስትራቴጂ ዛሬ ጳጉሜን 1 ጃካርታ ላይ ይፋ አደረጉ።።
ምጣኔ ሃብታዊው ስትራቴጂ የንግድ ማነቆዎችን መበጠስ፣ ነፃ የትምህርት ዕድሎችን መጨመርና የአቪየሽን መስክን ማስፋትን አክሎ አውስትራሊያ ከእስያ አገራት ሽርካነቷን የምታሳድግበትን 75 ምክረ ሃሳቦችን ያካተተ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖሊሲው ካለፉት አሠርት ዓመታት ወዲህ ይህ ትልቁ ቀጣናዊ የንግድ ትስስሮሽን የሚያሳድግ ምጣኔ ሃብታዊ ስትራቴጂ እንደሆነ ገልጠዋል።
በቀጣዩ አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥም የሙዋዕለ ንዋይ ፍሰትን ለማሳደግ $95.4 ሚሊየን ወጪ እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በፌዴራል መንግሥቱና ሕወሓት መካከል ኖቬምበር 2022 የግጭት ማቆም ስምምነት ከተደረሰ በኋላ ትግራይ ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ አሰቃቂ ድርጊቶች ይፈፀሙ እንደነበርና ምናልባትም በሰብዓዊነት ላይ የተፈፀሙ ወንጀሎች ሳይተገበሩ እንዳልቀረ ነሐሴ 29 ባወጣው ሪፖርቱ አስታውቋል።
ሪፖርቱ አክሎም፤ የኤርትራ መከላከያ ኃይሎች ሰላማዊ ሰዎች ላይ ታቅዶ የተካሔዱ ሕገ ወጥ ግድያዎችን መፈፀማቸውንና ስምምነቱ ከተፈረመም በኋላ ለወራት ሴቶችን በወሲባዊ ባርነት ይጠቀሙ እንደነበር አመልክቷል።
በማያያዝም፤ የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት፤ በኢትዮጵያ ተጠባቢ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት የወንጀሎችን ማስረጃዎች ጠብቆ እንዲያቆይና ለወደፊትም የተጠያቂነት ድጋፍ ጥረቶች እንዲያግዝ ውክልናን መልሶ እንዲቸር ጠይቋል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ቀዳሚ የምርምር ግኝቶቹን ሪፖርቱን ይፋ ከማድረጉ በፊት ለኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትና ለኤርትራ መንግሥት ነሐሴ 11 ማጋራቱን ጠቅሷል።
ሆኖም ሪፖርቱን ይፋ እስካደረገ ድረስ ከመንግሥታቱ በኩል የደረሰው ምላሽ እንደሌለም ገልጧል።
ድምፅ ለፓርላማ
የአውስትራሊያ ነባር ዜጎች ተጠባቢና አንቂ ማርስያ ላንግተን አውስትራሊያውያን የይሁንታ ድጋፋቸውን ለድምፅ ለፓርላማ እንዲቸሩ ጠየቁ።
ፕሮፌሰር ላንግተን ጥሪያቸውን ያስተላለፉት ዛሬ ጳጉሜን 1 ቀን በብሔራዊ ፕሬስ ክለብ ተገኝተው ድምፅ ለፓርላማን አስመልክተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ነው።
የድምፅ ለፓርላማ አካልን ምክረ ሃሳቦች ማድመጥ የአውስትራሊያ መንግሥት በትንሹ ሊያደርገው የሚችለው ግብር እንደሆነ ያመላክቱት ላንግተን፤ አውስትራሊያውያን ሕዝበ ውሳኔው ዙሪያ ካሉት ጫጫታዎች ወጣ ብለው ለድምፅ ለፓርላማ ዕውንነት የድጋፍ ድምፃቸውን እንዲሰጡ አበረታተዋል።